[...] «እሺ ስሚኝ።» እያለ ጓደኛዬ ኤፕሪል ምስጢር መናገር ስትፈልግ ወደፊት ዘንበል እንደምትለው ተጠጋኝ፤ የእሷ ምስጢሮች ግን ደህና ምስጢሮች ሆነው አያውቁም። ምስጢር ናቸው ለማለት እንኳን ይከብዳል። «እኔ እዚህ እንዳለሁ ለማንም ካልተናገርሽ ዓይኖችሽን ልፈውስልሽ እችላለሁ።»
«አትቀልድ ባክህ!»
ሁለት ጊዜ አይኖቹን አርገበገበ። «ለማድረግ እየሞከርኩ ያለሁት እኮ እሱን ነው።»
«እኔ ደግሞ የምልህ አትችልም ነው።»
«ለምን አልችልም?»
«እንግዲህ ከመነጽር ውጭ ዓይኖቼን አስተካክሎልኝ የሚያውቅ ሰው የለም።»
«አንዳንድ የምችላቸው ነገሮች አሉ። የምለውን ካደረግሽ ታዪአለሽ...»
«... ስለአንተ ለማንም ካልተናገርኩ ማለት ነው?»
«እሱ ነው ነገሩ፣ እዚያ ጋር ነው ጨዋታው።»
«ጨርሰህ እውር እንደማታደርገኝ እንዴት አውቃለሁ? እነዚያ እንደውም እየደወሉ የሆነ ነገር ካልገዛችሁ እንደሚሉን ሰዎች ቃልህ የውሸት ሊሆን ይችላል።»
ድጋሚ እንደለመደው ማስተባበሉን ጀመረ። «ምንም ያልጎዳኝ ፍጥረት ላይ እንዲህ ዓይነት ነገር አላደርግም።»
«ስለዚህ ብጎዳህ ኖሮ ዓይኖቼን ልታጠፋኝ ትችላለህ ማለት ነው?»
«እሱ መረጃ አሁን አያስፈልግሽም።»
«እና ዓይኖቼ ከፈወስክልኝ እና እኔ ለማንም ካልተናገርኩ ሜዳችንን ትተህ ትሄዳለህ?»
«በትክክል» [...]